ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 15 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በሶስተኝነት አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 15 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በሶስተኝነት አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጋና አክራ ከግንቦት 5 አንስቶ ሲካሄድ የቆየው 24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በአምስት ወርቅ፣ አራት የብር እና ስድስት የነሐስ በአጠቃላይ 15 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ውድድሩን ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
በአህጉራዊው መድረክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የገቡ አትሌቶች ባስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል በኩራት የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ማድረግ መቻላቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በውድድሩ ከፍተኛውን ክብር ያገኙትና የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉት አትሌቶች አትሌት አጃይባ አልዩ ፣ አትሌት ምስጋና ኃይሉ፣ አትሌት ገመቹ ጎዳና ፣አትሌት ምስጋናው ዋቁማ እና አትሌት ውብአለም ሽጉጤ ናቸው።
የብር ሜዳሊያ ስኬት ያስመዘገቡት አትሌቶችና ቡድኖች ደግሞ የ4 በ 400 ሜትር የሴቶች ሪሌ ቡድን፣ አትሌት ኦታጌ ኦባንግ፣ አትሌት ሙቢን ሀጂ እና አትሌት ሀጎስ እዮብ መሆናቸው ታውቋል።
በውድድሩ የነሐስና የክብር አሻራቸውን ያሳረፉት ቀሪዎቹ ስኬታማ አትሌቶች ደግሞ አትሌት አልማዝ ዮሐንስ፣ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው፣ አትሌት ዘይን አየልኝ፣ አትሌት በፀሎት አለማየሁ፣ አትሌት አሰፉ አብርሃ እና አትሌት አብዱልሰላም አብዱልዋሂብ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዚህ በአህጉሪቱ የስፖርት መድረክ ላይ በ32 ሴት እና በ31 ወንድ አትሌቶች፣ በአጠቃላይ 63 አባላትን በመያዝ ጠንካራ ተሳትፎ አድርጋለች።
የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ የበላይነት በአህጉሪቱ መድረክ ላይ ዳግም ያስመሰከረ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ኬንያ ስድስት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሰባት የነሐስ በድምሩ 17 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።
ደቡብ አፍሪካ በስድስት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ስድስት የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
ናይጄሪያ እና ኮትዲቭዋር አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ከተሳተፉ ሀገራት መካከል 25ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በካሜሮን ዱዋላ በተደረገው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት የወርቅ፣ አራት የብር እና አንድ የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አራተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ሻምፒዮና የሜዳሊያ ብዛት እና ደረጃዋን አሻሽላለች።