በወራጅ ቀጠና የሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ በኒውካስትል ዩናይትድ ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በወራጅ ቀጠና የሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ በኒውካስትል ዩናይትድ ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኒውካስትል ዩናይትድ ዌስትሃም ዩናይትድን 3 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዊሊያም ኦሱላ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኒክ ዎልትማደ ቀሪዋን ጎል ለኒውካስትል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቫለንቲን ካስቴላኖስ ለዌስትሃም የማስተዛዘኛውን ጎል አስቆጥሯል።
ባለሜዳው ኒውካስትል ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
በሊጉ 14ኛ ድሉን ያስመዘገበው ኒውካስትል ዩናይትድ በ49 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 19ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ዌስትሃም ዩናይትድ በ36 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። የለንደኑ ክለብ በሊጉ የመቆየት ተስፋው ተመናምኗል።
ማክሰኞ ቶተንሃም ቼልሲን ካሸነፈ ዌስትሃም ወደ ሻምፒዮንሺፑ ይወርዳል።
ዛሬ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ ኖቲንግሃም ፎረስትን 3 ለ 2 በማሸነፍ በ68 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱን አረጋግጧል።
ሰንደርላንድ ኤቨርተንን 3 ለ 1፣ ሊድስ ዩናይትድ ብራይተንን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ብሬንትፎርድ ከክሪስታል ፓላስ ሁለት አቻ ሲለያዩ ፉልሃም እና ዎልቭስ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።
የ37ኛ ሳምንት ነገም ቀጥሎ ሲውል የሊጉ መሪ አርሰናል ከበርንሌይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ከነገ በስቲያ ቦርንማውዝ ከማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።