ቀጥታ፡

ልማት የማያገኙ የነበሩ አካባቢዎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) 

ቦንጋ ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት አምስት አመታት ልማት የማያገኙ የነበሩ አካባቢዎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕስ መስተዳድር  ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በኮንታ ዞን ኮይሻ ወረዳ 142 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የንጽህ መጠጥ ውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት ከልማት የራቁ አካባቢዎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።


 

በዚህም የኮንታ ኮይሻ ወረዳ አንዱ መሆኑንና ማህበራዊ ተቋማትን በማዳረስ ህብረተሰቡ አገልግሎቶችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በበኩላቸው፤  ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ የውሀ ተቋማት ተገንብተዋል ብለዋል።


 

በዚህም ክልሉ ሲመሰረት የነበረውን ንፁሃ የመጠጥ ውሃ ሽፋን  በእጅጉ ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ዛሬ ለተመረቀው የኮንታ ኮይሻ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ 90 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው፤ በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ  የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።


 

ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶችም ለማህበረሰቡ የጎላ ጠቀሜታ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።

የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ወንድሙ፤  የውሀ ተቋሙ የኮይሻ ከተማ ማህበረሰብ ጥያቄን የመለሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

በለውጡ መንግስት የኮይሻ ወረዳ የውሃ፣ የመንገድ፣ የመብራት የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ መሆኗን ጠቁመዋል።    


 

በተመሳሳይ በወረዳው 52 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የደለባ አልፋ ቶልካ የመንገድ ፕሮጀክትም ተመርቋል።

መንገዱ 12 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና  ከሶስት በላይ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ መሆኑ ተመላክቷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም