ቀጥታ፡

በክልሉ ለማህበረሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል   

ቡኢ ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለማህበረሰቡ የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ከ56 ሺህ 750 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁለት ጤና ጣቢያና አንድ አጠቃላይ ጤና ኬላን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው።


 

በክልሉ ለማህበረሰቡ የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ  እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ለዚህም ስኬት ከማህበረሰቡ የሚነሱ የጤና ተቋማት፣ መንገድንና መብራት ጨምሮ ሌሎች የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ የመስጠት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው፤ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ የጤና ተቋማት ለማህበረሰቡ የጤና አገልግሎትን በብቃት ለመስጠት አጋዥ ናቸው ብለዋል።


 

በመንግስትና በማህበረሰብ ተሳትፎ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸዉ የአዴሌና የሱተን ጤና ጣቢያ እንዲሁም የዱግዳ ጤና ኬላ ከ56 ሺህ 750 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የእናቶችንና የህፃናት ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የጤና ተቋማቱ መጠናቀቅ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን እንደገለፁት፤ የጤና ተቋማቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው መንግስት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር የያዘውን አቅጣጫ እውን የሚያደርግ ነው።


 

በዞኑ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የጤና ተቋም ባለመኖሩ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በሶዶ ወረዳ ሱተን ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅነሽ አበበ ናቸው።

ዛሬ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጤና ጣቢያ ከዚህ ቀደም የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌላ ስፍራ በመጓዝ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ገልጸዋል።


 

በሌላ በኩል ርዕሰ መስተዳድሩ በሶዶ ወረዳ ሪፌንሶ ከተማ ለሚካሄደው የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት ግንባታ ስራ ማስጀመሪያ የመሰረተ ድንጋይ ያኖሩ ሲሆን በመርሐ ግብሩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም