ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጣቸው የላቁ አገልግሎቶች የሚደነቁ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን አየር መንገዱ ባዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ገለጹ። 

ተሳታፊዎቹ የዋና ከተማዋ የአዲስ አበባ ዘመናዊና ፈጣን እድገት እጅግ አስደናቂ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ አመት ምስርታ በዓልን በማስመልከት ባዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ በርካታ እንግዶች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች አስደናቂ ናቸው።

ከአሜሪካ የመጣችውና በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ካቲ ቴለር በመላው አውሮፓ፣ አሜሪካና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለምታደርጋቸው ጉዞዎች ሁልጊዜ የምትጠቀመው የኢትዮጵያ አየር መንገድን መሆኑን ገልጻለች።


 

አየር መንገዱ በሀገር ውስጥ፣ በአህጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም ያለውና እጅግ አስደሳች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑን በመግለጽ አድናቆቷን ችራለች።

የሩጫ ውድድሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበትና እጅግ ደማቅ ዝግጅት እንደነበር የጠቀሰችው አሜሪካዊቷ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ መሆኑንም ገልጻለች፡፡

ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው ብላለች።

የአዲስ አበባን ፈጣን ለውጥ በተመለከተም በየጊዜው አዳዲስ ግንባታዎችን፣ ዘመናዊ ሕንፃዎችንና አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን መመልከቷን አስታውቃለች፡፡

ከብራዚል የመጣችው ተሳታፊ ሊዲያ ቡርኖ በበኩሏ፤ ይህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ውድድር እንዳልሆነና ቀደም ሲል በሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ላይ መሳተፏን አስታውሳለች።


 

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበት የታደለች ሀገር መሆኗን የጠቆመችው ብራዚላዊቷ፣ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባም በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ ሳቢ ከተማ መሆኗን ገልጻለች።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደጋጋሚ መጓዟን እና የአየር መንገዱ አገልግሎት እጅግ አስደናቂና በጣም የሚያኮራ መሆኑን ጨምራ ተናግራለች።


 

ሁልጊዜ ከጃፓን ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ቀዳሚ ምርጫችን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፤ የበረራ አባላቱን ጨምሮ እያንዳንዱ የአየር መንገዱ ሰራተኛ  ሙያዊ ስነ ምግባሩ የላቀ ነው ሲል  የገለጸው ደግሞ ጃፓናዊው ዲያላስ ኒዩሳኮ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም