ለፍትህ ስርዓት መጠናከር ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉልህ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለፍትህ ስርዓት መጠናከር ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉልህ ሚና አላቸው
አርባምንጭ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገሪቱ ፍትህ ስርዓት መጠናከር ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉልህ ሚና እንዳላቸው የፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 10ኛው ሀገር አቀፍ የምስለ ችሎት ውድድር ከግንቦት 7 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሄዶ ተጠናቋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ መንግስት የፍትህና የዳኝነት ተቋማትን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፍትህ አገልግሎትን በዲጂታል ስርዓት ለማገዝ፤ ባለጉዳዮች ባሉበት ሆነው ያለ ምንም የአካል ንክኪ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ መሰል የምስለ ችሎት ውድድሮች የሀገሪቱን የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በመቅረጽ እውነትን የመፈለግ እና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራዎችን በትኩረት እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
በተለይም ለፍትህ ስርአት መጠናከር እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ባለሙያዎችን በማፍራቱ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉልህ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።
ሀገራዊ የምስለ ችሎት ውድድሩ ተማሪዎች የህግ ዕውቀት፣ የክርክር ብቃትና የሙያ ስነ-ምግባር እንዲያዳብሩ ይረዳል ያሉት ደግሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አብደላ ከማል(ዶ/ር) ናቸው።
ከተወዳዳሪ ተማሪዎች መካከል የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ አብርሃም ወርቁ ሀገር አቀፍ የምስለ ችሎት ውድድሩ በንድፈ ሃሳብ የቀሰምነውን ዕውቀት በተግባር እንድንፈጽም ብሎም የትንተና እና የሙግት ችሎታችንን እንድናዳብር አግዞናል ብሏል።
በሀገር አቀፍ የምስለ ችሎት ውድድር መርሃ-ግብሩ በ12 ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የህግ ተማሪዎች የተወዳደሩ ሲሆን አርባምንጭ፣ ሰላሌ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ከአንደኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል።