ቀጥታ፡

የባህል ሳምንቱ የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ የባህል ሳምንቱ ለተለያዩ የባህል ልምድ ልውውጦች ዕድል የሰጠና የእርስ በዕርስ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህል ሳምንት ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡ 

"የባህል ልማት ለኅብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ  ግንቦት 6 ቀን የተጀመረው ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ሳምንት ነገ ይጠናቀቃል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን የባህል ትርኢት ከማሳየት ባለፈ በሕዝቦች መካከል ትስስርን በመገንባት የጋራ እሴቶችን ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው፡፡ 

ኢዜአ ያነጋገራቸው ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የባህል ምግቦችን ይዘው የቀረቡ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ሀገር አቀፍ የባህል ሳምንቱ የተለያዩ የባህል ልምድ ልውውጦች የሚያገኙበት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ከኦሮሚያ ክልል የባህል ምግቦችን ይዛ የቀረበችው ሀዊ እጅጉ፤ የባህል ሳምንቱ መዘጋጀቱ የተለያዩ አካባቢዎች የባህል ምግቦች እንዲተዋወቁ የሚያስችል መሆኑን ትገልጻለች፡፡ 

በተለይም እንደዚህ አይነት የባህል ሳምንቶች መኖራቸው የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጨምራ ገልጻለች፡፡ 

ከአማራ ክልል የባህል ምግቦችን ይዛ የቀረበችው ኢሌኒ እንየው፤ የባህል ሳምንቱ ዜጎች ባህሎቻቸውን የሚያውቁበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ትገልጻለች፡፡

ከሲዳማ ክልል የባህል ምግቦችን ይዞ የቀረበው ይርጋለም መንግስቱ በበኩላቸው፤ ይዘናቸው የቀረብናቸው ባህላዊ ምግቦች ክልሉን ይበልጥ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

የባህል ሳምንቱ የተለያዩ የገበያ ትስስርና የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ነው ያለችው ደግሞ ከአዲስ አበባ የባህላዊ የወይባ ጢስ ይዛ የቀረበችው ካሚላት አህመድ ናት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም