ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እየተወጣን ነው-ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እየተወጣን ነው-ተፎካካሪ ፓርቲዎች
ጎንደር፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፉክክርና በትብብር ላይ ተመስርቶ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን በጎንደር ከተማና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ አቶ የዝናወርቅ ታደለ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየተሻሻለ መምጣቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዓላማና ፕሮግራሞቻቸውን ወደ ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረላቸው ነው።
ፓርቲያቸው በመጪው ምርጫ በሕዝብ ድምፅ አሸንፎ የፓርላማ ወንበር ለመያዝ የሚያስችለውን የምርጫ ቅስቀሳ በነፃነት እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ፓርቲ ተወካይ አቶ ደሴ ዓለሙ በበኩላቸው፤ መጪው ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው በትብብርና በፉክክር መርህ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ መገለጫ ሰላማዊ የፓርቲዎች የምርጫ ውድድር በመሆኑ፣ ፓርቲያቸው የምረጡኝ ቅስቀሳዎችን ያለአንዳች ተፅዕኖ እያካሄደ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ኃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተገኑ ደረጀ በበኩላቸው፤ ዴሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚገነባ ሂደት ባለመሆኑ፣ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በስፋት እንዲጠቀም ስለ ምርጫው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቀራርበው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው፤ ለምርጫው ስኬታማነት የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በየጊዜው ተቀራርቦ በውይይትና በንግግር በመፍታት፣ ለምርጫው አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር በኩል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በጋራ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በምርጫው ለመወዳደር የተመዘገቡ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ሆነዋል።