ቀጥታ፡

የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካን ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፡- በጎዴ እየተገነባ የሚገኘውን የማዳበሪያ ፋብሪካ በአጠረ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን የኢትዮጵያን አንዱን ቁልፍ ችግር እንፈታለን የሚል እምነት ይዘን እየሠራን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በጎዴ ተገኝተው የማዳበሪያ ፋብሪካው የግንባታ ሥራ የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም የፕሮጀክት ስፍራውን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት ማብራሪያም፤ በዚህ ቦታ መገኘታችን ይህ ፕሮጀክት በቅርበት የምንከታተለው፣የምናየው፣ የምንመራው፣ችግሮች ካሉ እየቀረፍን ከተቻለ አፍጥነን ካልሆነም ባልነው ጊዜ ለመጨረስ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በመላው የፕሮጀክቱ ስፍራ የሚታየው የሥራ ሂደት ፍጥነት አበረታች መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ከዳንጎቴ ጋር የነበረን ስምምነት በጎዴ 3 ሚሊየን ቶን ማዳበሪያ ማምረት የሚችል ፋብሪካ መገንባት ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤በዚሁ ወቅትም ለሕዝባችን የገባነው ቃል ፋብሪካው በ40 ወራት ይጠናቀቃል የሚል ነበር ብለዋል።

አሁን እየሠራን ያለነው ግን በተቻለ መጠን ከ40 ወራት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ነው፤በዚህም መሠረት ለእኛም ገበያ ከእኛ የሚተርፍ ካለም ለውጭ ገበያ ለመጠቀም እየሠራን ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ያኔ ሐሳብ ነበር፤አሁን ግን በተግባር እየተሠራ ነው፤ቢበዛ ከአራት ወራት በኋላ ስንመጣ አብዛኛው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ይጠናቀቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዚህም መሠረት ለ5 ሺህ ሰው የሚሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታ (ትንሽ መንደር) ይሠራል ነው ያሉት።

በአካባቢው ያለውን ውኃ ወደ ግንባታ ስፍራው አካባቢ የማምጣት፣ ከፍተኛ ቦታዎችን ዝቅ የማድረግና ዝቅተኛ ቦታዎችን ከፍ አድርጎ የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ለቀጣይ ሥራውም በርካታ ሪሶርስ (ግብዓት) ተገዝቶ እየመጣ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በአጠረ ጊዜ ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካውን አጠናቅቀን የኢትየጵያን አንዱን ቁልፍ ችግር እንፈታለን የሚል እምነት አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሊኮ ዳንጎቴ በጣም ቁርጠኛ ሰው መሆናቸውን፤በገቡት ቃል መሠረት ገንዘባቸውን፣ጊዜያቸውን እና ሙያተኞችን በስፍራው ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ፕሮጀክቱን በማሳካት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዋነኛውን ችግር ለመፍታት እየተጉ መሆናቸውን በመጠቆም፤ እስካሁን በጣም ደስ የሚል ሥራ ማየታቸውን አንስተዋል።

በዚሁ መልክ የክልሉ ብሎም የፌዴራል መንግሥት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንዲጠናቀቅ ካደረግን በጣም ትልቅ ችግር የሚፈታ ፕሮጀክት ይሆናል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።

ጎዴ አካባቢ የምናደርጋቸው ኢንቨስትመንቶች ተደማምረው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ለኢትዮጵያ የሚያስገቡ ናቸው ሲሉም አስረድተዋል።

በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉት ቀላል ኢንቨስትመንት እንዳልሆኑ ገልጸው፥ አሊኮ ዳንጎቴ ብቻ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው እዚህ የሚያፈስሱት ብለዋል።

በአጠቃላይ በጣም ትልቅ የሀገርን መልክ፣ቁመና እንዲሁም የኢኮኖሚ ዐቅም የሚቀይር ኢንቨስትመንት በአካባቢው መኖሩን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም