በሦስቱ ክልሎች ትብብር የሕዝቡን የጋራ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሦስቱ ክልሎች ትብብር የሕዝቡን የጋራ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ነው
አሶሳ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ትብብር የሕዝቡን የጋራ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑ ተገለጸ።
በአሶሳ ከተማ የተገነባው የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች የጋራ ሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
ክልሎቹ የሚጋሯቸውን አዋሳኝ አካባቢዎች የልማትና የሰላም ቀጠና ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም የሕዝቡን ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዳደረሱት ተመልክቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሦስቱ ክልሎች በጋራ እያከናወኗቸው የሚገኙት የሰላምና የልማት ሥራዎች በክልሎቹ መካከል ትብብር እንዲጎለብት አድርገዋል።
የሕንጻው ግንባታ በክልሎቹ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የሦስቱ ክልሎች የሰላምና የልማት ትብብር የመደመር አስተሳሰብን በተግባር የሚያሳይ እና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በሦስቱ ክልሎች መካከል እየተገነባ ያለው የመሠረተ ልማት እና የሰላም ጥበቃ ስራ የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነትን ይበልጥ እያጠናከረ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በተለይም የጋራ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሰላም እሴት ግንባታና በሕዝባዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም በሦስቱ ክልሎች መካከል ለሚኖረው ጠንካራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አስተማማኝ መሠረት መጣሉን ጠቅሰዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሦስቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በክልሎቹ መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በአሶሳ ከተማ የተገነባው የሦስቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለ አራት ወለል ሕንጻ ሲሆን ግንባታው 300 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም ተገልጿል ።