የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ዳግም ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ዳግም ሊጀመር ነው
ኮምቦልቻ ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታን ዳግም ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች በኮምቦልቻ ጣቢያ በመገኘት የባቡር መስመሩን ግንባታ ዳግም ለማስጀመር የሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ስለሽ ካሳ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጋር በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስር የመፍጠር አቅም አለው።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው፣ አሁን ላይ የጥገናና የመልሶ ግንባታ ሥራውን በይፋ ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅትም የሰው ኃይል የማሟላት፣ የማደሪያ ቤቶች ጥገና እና የመሠረተ ልማት ማመቻቸት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ሥራውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በአራት ቡድን ተከፋፍሎ ርብርብ እንደሚደረግ አመልክተው፣ አጠቃላይ ግንባታውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የንግድ ሥርዓቱን ለማሳለጥ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ቀጣናዊ ምጣኔ ሀብትን ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ መቋረጥ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ ዳግም ለመጀመር የተደረገው ዝግጅት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ግንባታው በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን፣ "የፕሮጀክቱን ዳግም መጀመር የዞኑ ሕዝብ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ በመሆኑ፣ ለሥራው ስኬታማነት የዞኑ አስተዳደርና ሕዝብ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁና ቁርጠኛ ነው" ብለዋል።
በተመሳሳይ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር፣ "የባቡር ፕሮጀክቱ ዳግም መጀመር ለሕብረተሰቡ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የሚመረቱ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በቀላሉ ወደ መሃል አገርና ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ፣ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በፍጥነትና በብዛት ለማጓጓዝ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል።
"ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪና የሎጅስቲክስ ከተማ በመሆኗ፣ የባቡር መስመሩ መነቃቃት ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ጥቅም አለው'' ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ ናቸው።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት አጠቃላይ ርዝመት ከ390 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ 51 ድልድዮች እና 12 ዋሻዎች እንዳሉት ተመልክቷል።
በተጨማሪም ስምንት የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እንዳሉትም ታውቋል።