በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የተጀመሩ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የተጀመሩ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት ይጠናከራሉ
ጭሮ ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በብልፅግና ፓርቲ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የተጀመሩ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት ይጠናከራሉ ሲሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ አስታወቁ።
የፓርቲው የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሐግብር ዛሬ በዞን ደረጃ በጭሮ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እና የፓርቲው ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ እንደገለጹት፤ ፓርቲው ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንካራ መሠረት በመጣል የብልፅግና ብርሃን እንዲፈነጥቅ አድርጓል።
ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ብቻ 108 የጤና ተቋማት እና 5 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ማኅበረሰቡን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ፓርቲው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግልጽ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪዋ፤ በገጠርና በከተማ ዜጎችን ከድህነት የሚያወጡ ልዩ ልዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንና በቀጣይም ይህ ስኬት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር ባለፉት ዓመታት ተጨባጭ የሆኑ የልማት ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው የልዩነት ምንጭ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን በወል ትርክቶች በመቀየር ለሕዝቦች አንድነት ከፍተኛ ሥራዎችን ሰርቷል ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል እኩል የፖለቲካ ተሳትፎን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ የፓርቲው አባላትና የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ብልፅግና ፓርቲ የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ቃሉን በተግባር መተርጎም መቻሉን አንስተዋል።
በተለይም በከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የአካባቢን ገጽታ በፍጥነት ከመቀየር ባለፈ፣ ለአዲስ የሥራ ባህል መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት አርሶ አደሩን ቀጥተኛ የልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ ሕይወቱን እንዲቀይር ረድቶታል ነው ያሉት።
በተለይም በበጋ ስንዴ ልማት እየተሰራ ያለው ታሪካዊ ሥራ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ከመጨመሩም በላይ የአርሶ አደሩን ገቢ በእጅጉ አሳድጓል ብለዋል።
በጭሮ ከተማ በተካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሐግብር ላይ ከዞኑ ልዩ ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።