ቀጥታ፡

የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር

በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን።

👉የግንቦት - ታላቁ ሁነት

የምርጫ ጉዳይ ወቅታዊና ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ በሁሉም አካባቢዎች የዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የቀጠለበት ሳምንት ነው።

መራጮች ካርዳችንን ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተመቻቸላቸው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ማኒፌስቷቸውን እያስተዋወቁ ቀጥለዋል።

የተለያዩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት በመስጠት ሙያዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

ለዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሰማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

👉የመጠጥ ውሃ ችግሮችን የመፍታት ጥረት ማሳያዎች

በሳምንቱ በወላይታ ዞን ከ150 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሆቢቻ ወረዳ ብዝሃ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ፕሮጀክቶቹን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) መርቀዋል። የፕሮጀክቶቹ ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃት ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የላቀ ትርጉም እንዳለው ተነስቷል።

በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በቀብሪደሃር ከተማ በ407 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄድ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ አስጀምረዋል። 

ከለውጡ በኋላ በክልሉ ከ370 በላይ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። በዚህም የመጠጥ ውሃ ሽፋኑ ከ19 ወደ 52 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ታውቋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞንም የደደር ከተማንና የአካባቢውን ማህበረሰብ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ታስቦ የተገነባው ፕሮጀክትም ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው በዚሁ ሳምንት ነበር።

የፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ሃላፊ መሰረት አሰፋ፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እና ሌሎችም የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ደደር ከተማን ጨምሮ ሌሎች በወረዳው ሶስት ቀበሌዎች የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።

👉የጤና ጉዳይ

የጤና ሚኒስቴር የተቀናጀ የህክምና እና የምርመራ ዘመቻ ከግንቦት 3 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በስምንት ክልሎች በሚገኙ 154 ወረዳዎች የሚያካሄድ መሆኑ የተገለጸውም በዚሁ ሳምንት ነበር። ይሄው መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

መርሃ ግብሩ በተለይም ትምህርት ቤቶችን ማዕከል በማድረግ የሚከናወን ሲሆን ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል አላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

👉ከተረጂነት ወደ ምርታማነት 

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው የውይይት መድረክም የሳምንቱ አበይት ጉዳይ ነበር።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት የመውጣት ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ልማት በተለይም የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተመዘገበውን የላቀ ስኬት ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሌሎች የተለያዩ የግብርና የልማት ስራዎችንም በተጠናከረ መልኩ በማከናወን ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ ከተረጂነት የመውጣት ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅም አካል ሆኖ የመንግስት ስትራቴጂክ አጀንዳ ተደርጎ በፖሊሲ አቅጣጫ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ምርታማነትን በማሳደግ የሀገርን ብልጽግና እውን በማድረግ የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ መቀየር ይኖርብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው ግብ እንዲሳካ በቂ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ሚዲያ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው ኢዜአ ይህንን ሀገራዊ ትልም ለማሳካት የይዘት ስራዎችን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

👉የምግብ ስርዓት ሽግግር

በጋምቤላ ክልል ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው የምግብ ስርዓት ሽግግር እና የኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጋምቤላ ከተማ በይፋ የተካሄደውም በዚሁ ሳምንት ነው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር)፤ በክልሉ የተሟላ ስርዓተ ምግብን በማረጋገጥ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

👉ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በአሶሳ

በአሶሳ ከተማ ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የተጀመረው በዚሁ ሳምንት ነው። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ የትምህርት ቤቱን ግንባታ አስጀምረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን 34 ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ መሆኑን ያስታወሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ በአሶሳ ከተማ የሚገነባው ትምህርት ቤትም በአንድ ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።

👉የሰላምና አብሮነት እሴት ግንባታ

የሐረሪ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና የማያ ከተማ አስተዳደር "የህዝቦች ሰላምና አብሮነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ የህዝብ ለህዝብ የሰላምና አብሮነት ኮንፍረንስ የተካሄደውም በዚሁ ሳምንት ነው።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ የሐረርጌ ህዝቦች ትስስር በሀገሪቱ የታሪክ ማህደር ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጠውና ለታላቅ ማህበራዊ ውህደት ተምሳሌት እንደሚሆን ገልጸዋል። 

የኮንፈረንሱም ዓላማ የሰላም እሴት ግንባታና የልማት ትስስርን ይበልጥ ማጠናከር ስለመሆኑ አንስተዋል።

👉የግብርና ልማትና ምርታማነት

በአማራ ክልል ለዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ81 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ያስታወቀው በዚሁ ሳምንት ነው።

የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ለማሻሻል ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ከ76 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ81 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ኮምፖስት መዘጋጀቱ ታውቋል።

👉በኦሮሚያ ክልልም ለዘንደሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካል የሆነው ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአቮካዶ ተክል እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ኃላፊ ሙሐመድሳኒ አሚን፤ በመጪው ክረምት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም አቮካዶን ጨምሮ አስር አይነት የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች ስለመዘጋጀታቸውም ተናግረዋል።

በተለይም አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን፣ ፓፓያ፣ ግሽጣ፣ ብርቱካን፣ አፕል፣ ሎሚና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መዘጋጀታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

በክልሉ የአቮካዶ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በማዳቀል የችግኝ ዝግጅት ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

በክልሉ እስካሁን ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመደበኛና በተሻሻሉ የአቮካዶ ችግኞች መሸፈኑንም ገልጸዋል።

👉የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ በክልሉ ሎካ አባያና ደራራ ወረዳዎች በበልግ ወቅት በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን የበቆሎ ማሳ በመስክ የተመለከቱትም በዚሁ ሳምንት ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የሰብል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን የሚያረጋጋ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ውጤት እየተገኘ ነው።

በዚህም በበልግ ወቅትም ፆም የሚያድር መሬት እንዳይኖር በማድረግና ግብአቶችን በወቅቱ በማቅረብ እየተከናወነ ባለው የእርሻ ስራ የምርት ቁመናው ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበልጉ ያለውን  አመቺ የዝናብ ስርጭት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦት በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት አሁን ላይ ለማሳ እንክብካቤ ስራ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

👉የኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በኮምቦልቻ ከተማ ተገኝተው የመረቋቸው የምግብ ዘይት እና የቆርቆሮ ማምረቻ ፋብሪካዎች ሥራ የጀመሩትም በዚሁ ሳምንት ነው።

የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሙሄ፤ በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ልማት ይበልጥ እያንሰራራ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ በድምሩ 69 አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ገልጸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረትና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን በመተካት ከፍተኛ የሃብት ምንጭ እየሆኑ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም