ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የችግኝ ዝግጅትና አቅርቦት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ ዘንድሮ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የችግኝ ዝግጅትና አቅርቦት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲተገበር ቆይቷል።

በመርሀግብሩ  እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል። 

ይህ ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክት በኅብረተሰቡ ዘንድ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ በጎ ባህል እንዲዳብርና የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እንዲያድግ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። 


 

በተለይም በችግኝ ማፍላት፣ በተከላና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በችግኝ ዝግጅት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዳሉት፣ ዘርፉ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ድርሻ እንዲያበረክቱ አስችሏል።

በየካ ክፍለ ከተማ ሱስኒ ችግኝ ጣቢያ በችግኝ ዝግጅት ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ሥራ ምናለ፣ ጣቢያው በአካባቢያቸው መኖሩ የሥራ ዕድል እንዳስገኘላቸውና የሥራው ዓላማና ግብም ሂደቱን በደስታ ለማከናወን እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ ወይዘሮ ፅጌ ነጋአብ በበኩለቸው፣ ያዘጋጇቸው ችግኞች በተለያዩ ቦታዎች ተተክለው ከተማዋን ውብ፣ አረንጓዴና ነፋሻማ ሲያደርጉ መመልከት ደስታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።


 

ሥነ-ምህዳሩ የተጠበቀ አካባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ሀገራዊ ተልዕኮ ውስጥ የራሳቸውን በጎ አሻራ እንዲያኖሩ እያስቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ራሔል ዮሐንስ ናቸው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፉ፣ የከተማ አስተዳደሩ ማስተር ፕላኑን ተከትሎ የከተማዋን አረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ያለሙ ተግባራትን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ይህንን ግብ ለማሳካትም በቢሮው ሥር በሚገኙ ዘጠኝ የችግኝ ጣቢያዎች እና በዘርፉ በተሰማሩ 285 ማኅበራት አማካኝነት ከፍተኛ የችግኝ ዝግጅትና አቅርቦት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። 

በተለይም በከተማዋ ዘንድሮ ለተከላ ከሚዘጋጁት ችግኞች መካከል ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም