ብልፅግና ፓርቲ ዘመናት ላስቆጠሩ የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ችሏል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ዘመናት ላስቆጠሩ የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ችሏል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
ሰመራ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ድምፅ በትዕግሥት በመስማት ዘመናት ያስቆጠሩ የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በተግባር ምላሽ መስጠት የቻለ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሠመራ ከተማ አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት የምርጡኝ ቅስቃሳ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በዕለቱ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲው ስራ አሰፈፃሚ አባል አወል አርባ እንዳሉት፤ ፓርቲው የአፋርን ህዝብ የመልማት ጥያቄ መመለስ ችሏል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፓርቲው ያስመዘገባቸውን ዘርፈ-ብዙ የልማት ስኬቶች ይበልጥ በማጠናከር፣ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነትና በትጋት እንሰራለን ብለዋል።
በለውጡ መንግሥት በተፈጠረው ምቹ ሥርዓት ምክንያት በሕዝቦች መካከል ያለው ነፃነት፣ አንድነትና እኩልነት ይበልጥ እየጎለበተ መጥቷል ነው ያሉት።
የአፋር ሕዝብ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በጋራ ሲያነሳቸው የነበሩት ጥያቄዎች በለውጡ መንግሥት ምላሽ ማግኘት ችለዋል፤ ይህም የሚያሳየው ፓርቲያችን በህዝብ የተገነባና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የቆመ መሆኑን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ፓርቲው የአፋር ሕዝብ በሀብቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት ከመዘርጋቱም በላይ፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝም በተግባር እንዲረጋገጥ አድርጓል ሲሉም አክለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በመደመር ፍልስፍና ላይ በመመስረት የህዝቦችን ዘላቂ አንድነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚተጋ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቅስቀሳ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊም በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየዘርፉ ማኅበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ በቁርጠኝነት እየሠራ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በከተሞች አካባቢ በስፋት እየተተገበሩ ያሉትን የኮሪደር ልማት ስራዎች እንደ ዋነኛ ማሳያ የጠቀሱት ከንቲባው፤ ብልፅግና ፓርቲ ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረጉና የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ የልማት ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።