ቀጥታ፡

በወሰድነው ካርድ ሀገርን ለማሳደግ ይሰራል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል 

ጅማ ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በወሰዱት ካርድ ሀገርን ለማሳደግ ይሰራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን እየጠበቁ መሆኑን የጅማ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተመቻቸላቸው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ማኒፌስቷቸውን እያስተዋወቁ ቀጥለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጅማ ዞን ነዋሪዎችም ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የኦሞ ናዳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሳሊያ ዩሱፍ እንደተናገሩት፤ ምርጫ በድምፅ የሀገርን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል በመሆኑ፣ በዕለቱ ሀገርን ያሳድጋል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

ሁሉም የምርጫ ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች በዕለቱ ወጥተው ላመኑበት ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጡና እንዲመርጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሌላኛው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሀመድ ሼኽ ከድር በበኩላቸው፤ በወሰዱት የምርጫ ካርድ ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን ተገንዝበው ሌሎችንም እያነቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጅማ ከተማ ነዋሪው ወጣት ወንድወሰን አሰፋ ምርጫ ለዴሞክራሲ መሠረት የሚጥልና የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመወሰን የሚረዳ በመሆኑ፣ ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በዕለቱ ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም