የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ስኬታማ ተግባራት ከአፍሪካ ቀዳሚው የአየር መንገድ መሆን ችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ስኬታማ ተግባራት ከአፍሪካ ቀዳሚው የአየር መንገድ መሆን ችሏል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ስኬታማ ተግባራት ከአፍሪካ ቀዳሚና ግዙፍ የአየር መንገድ መሆን መቻሉን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አየር መንገዱ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት አስመልክቶ ያዘጋጀው የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
በሩጫ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህንን ጨምሮ የአየር መንገዱ የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በልዩ ድምቀት የተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ መነሻውን ከፑሽኪን አደባባይ (ሣር ቤት) በማድረግ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማጠናቀቂያውን አድርጓል።
በውድድሩ አትሌቶች፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች፣ የስፖርት ቤተሰቡና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፣ ተቋሙ በታሪኩ መጀመሪያ በ1938 ዓ.ም ስራ ሲጀምር በጥቂት አነስተኛ አውሮፕላኖች ብቻ በረራ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባደረገው ያልተቋረጠ እድገት፣ በአሁኑ ወቅት የዓለምን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያካተቱ የተለያዩ የቦይንግ፣ የኤርባስ እና የሌሎች አውሮፕላኖች ባለቤት መሆን መቻሉን አብራርተዋል።
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ145 በላይ መዳረሻዎች እንዳሉት የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ በተለይም በካርጎ፣ በአቪዬሽን አካዳሚ ማሰልጠኛ እና በሌሎችም የዘርፉ አገልግሎቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ይህ መዋቅራዊ ጥንካሬውና ስትራቴጂካዊ ዕድገቱ አየር መንገዱን ተመራጭና ቀዳሚ እንዲሆን እንዳስቻለውም አመልክተዋል።
አየር መንገዱ የ80 ዓመት ታሪካዊ የስኬት ጉዞውን የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫን ጨምሮ በፓናል ውይይቶች፣ በአውደ-ርዕዮች እና በተለያዩ ማህበራዊ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት እያከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎዳና ሩጫው ዋና ዓላማ ተቋሙ ባለፉት ሰማንያ ዓመታት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ለመዘከር፣ የቀድሞ ሠራተኞችንና ደንበኞችን ለማመስገን እንዲሁም የስፖርቱን ቤተሰብ ባሳተፈ መልኩ በጋራ ለማክበርና ዕውቅና ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ የጎዳና ውድድር የአየር መንገዱን ተሻጋሪና በጎ ገጽታ ይበልጥ ለማጉላት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በውድድሩ ላይ የተሳተፉት አቶ ዓለምወሰን አምባዬ እና ባቱ እምሩ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተመራጭ እና የሀገር የኩራት ምንጭ መሆናቸውን ገልጸው፤ በሩጫው በመሳተፋቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።