ዋንጫውን ማን ያነሳል? ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ? - ኢዜአ አማርኛ
ዋንጫውን ማን ያነሳል? ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ?
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።
ጨዋታው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 21 ድሎችን ሲቀዳጅ የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 71 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስምንት ጎሎችን ብቻ አስተናግዷል። ንግድ ባንክ በ66 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ እና አነስተኛ የጎል መጠን ያስተናገደ ቡድን ነው።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዘመኑ 25 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ21ዱ ሲያሸንፍ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
በ24ቱ ጨዋታዎች ላይ 52 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን ተቆጥረውበታል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 66 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 63 እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ 41 የግብ ክፍያ አላቸው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ ለስድስተኛ ተከታታይ የውድድር ዓመት ዋንጫውን ያነሳል። በአጠቃላይ ለዘጠነኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሊጉን ለማሸነፍ የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ ይኖርበታል።
ቡድኑ ካሸነፈ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳል።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በ24 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የምትመራው የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን፣ በ20 ግቦች የምትከተለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በጨዋታው ትኩረት ያገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማህሌት ምትኩ ጎል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሐ ግብር መቻል ከአዲስ አበባ ከተማ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቻል በ55 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ መውረዱ የተረጋገጠው አዲስ አበባ ከተማ በ15 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጨረሻ ሳምንት የሆነው የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከ25ኛ ሳምንት በፊት አስቀድሞ ተደርጓል።
የመርሐ ግብሩ ቅያሬ ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።