የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአዘጋጇ ሞሮኮ ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአዘጋጇ ሞሮኮ ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ መርሐ ግብር ሞሮኮ ኢትዮጵያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ማምሻውን በመሐመድ ስድስተኛ ስፖርት አካዳሚ በተካሄደው ጨዋታ ዳዊት ካሳው በ24ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ኢትዮጵያ መሪ ሆናለች።
ከእረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ መሐመድ ሙስታሽ ሞሮኮን አቻ ያደረገችውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ኢምራን ታላይ በ91ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ሞሮኮን አሸናፊ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር የሚችልባቸውን እድሎች መጠቀም አልቻለም።
ብሔራዊ ቡድኑ ውጤቱን ተከትሎ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በመጀመሪያ ጨዋታው ከግብጽ ጋር አቻ መውጣቱ ይታወቃል።
አዘጋጇ ሞሮኮ በስድስት ነጥብ ምድብ አንድን እየመራች ነው።
ሞሮኮ የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ናት።
ዛሬ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ግብጽ ቱኒዚያን በማሸነፍ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከቱኒዚያ ጋር ያደርጋል።
ቡድኑ በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የማለፍ ተስፋውን ለማለምለም ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።
ሞሮኮ ከግብጽ ሌላኛው የሚደረግ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ነው።