ቀጥታ፡

የምስራቅ ሐረርጌ ህዝብ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ ልማት ስኬት በተሞክሮነት የሚቀመር ተምሳሌታዊ ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ ሐረርጌ ህዝብ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ ልማት ስኬት በተሞክሮነት የሚቀመር ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለግብርና ምርታማነት ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳ የተከናወነው አስደናቂ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ተፋሰስ ልማት ስኬትም በምርጥ ተሞክሮነት ሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ መጠነ ሰፊ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ተፋሰስ ልማት ሥራም ከ18 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት መልማቱን ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ በማላቅ ከ38  ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬት እንዲያገግም ያስቻለ ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በትጋት እየሰሩ ለሚገኙ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ይህም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና በማጉላት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንድትገነባ እያስቻላት መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ተፋሰስ ልማት ሥራን የበለጠ በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም