ቀጥታ፡

ፋሲል ከነማ ወደ ድል ተመልሷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ታምራት ኢያሱ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ቃልኪዳን ዘላለም ቀሪዋን ጎል ለፋሲል ከነማ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የፋሲል ከነማው አብዱልአዚዝ አማን በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠረው ጎል ለአዳማ ከተማ ብቸኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ፋሲል ከነማ በ46 ነጥብ ደረጃውን ከስምንተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉም 11ኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ በበኩሉ ከነበረበት 15ኛ ደረጃ ወደ 16ኛ ዝቅ ብሏል።

ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ የ32ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሃዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የጨዋታዎቹን መጠናቀቅ ተከትሎ 32ኛ ሳምንት ፍጻሜውን አግኝቷል።

የ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም