ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለን ያመንበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል -የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለን ያመንበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል -የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለው የሚያምኑበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የምርጫ ካርድ የወሰዱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ተካሂዶ ተጠናቋል።
በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ድምፅ መስጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርስቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም አጠናቋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
መራጮችም በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችለቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው መራጮች እንዳሉት፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫና የሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥ መመረጥ መብት ማረጋገጫ መሳሪያ ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ፍቃዱ ለታ፤ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችለኝን ካርድ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ምርጫ ጣቢያ ወስጃለው ብሏል።
የፓለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና በመገናኛ ብዙኅን የሚያቀርቡት የፖሊሲ አማራጭ አስተምህሮ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ መምረጥ የሚያስችል ግንዛቤ እየሰጣቸው መሆኑን ገልጿል።
በዚህም የፓርቲዎችን የቀጣይ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ መረዳት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል ለሚለው ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት እያዘጋጃቸው መሆኑን ተናግሯል።
ዜጎችም በምርጫው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የሚያጎለብት ተሳትፎ በማድረግ ላመኑበት ፓርቲ ድምፅ መስጠት እንዳለበት አስገንዝቧል።
ሙሉጌታ አለሙ በበኩላቸው፤ በጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ምርጫ ጣቢያ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
በሚቀጥለው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት ዕለትም ለሀገር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ምርጫ ጣቢያ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የገለጹት ካሚል ሃምዛ፤ በምርጫው ወቅት ለሀገር ዕድገትና አንድነት ለሚሰራ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሰባት የምርጫ ጣቢያ የመራጭነት ካርድ የወሰዱት ኤልሳቤት ሙሉጌታ ናቸው፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር የምርጫ ጣቢያ የምርጫ ካርድ የወሰዱት ሽፈራው ሰራልኝ፤ ለሀገር ጥሩ ይሰራል ብለው ያመኑበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡