ቀጥታ፡

የጤና ምሩቃን ሰብአዊነትና ርህራሄን በመላበስ የሰውን ሕይወት መታደግ አለባቸው

ጎንደር፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፡-የጤና ተመራቂዎች ሰብአዊነትና ርህራሄን በመላበስ በሕክምና ሙያቸው የሰውን ልጅ ሕይወት ለመታደግ ሁልጊዜም መትጋት እንዳለባቸው ተገለጸ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ ለ41ኛ ጊዜ በሕክምና ሙያ ያሰለጠናቸውን 444 የሕክምና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡


 

በምረቃው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሸናፊ ታዘበ እንደገለጹት፣ ተመራቂዎች የሕክምና ስነምግባርና መርሆዎችን በማክበር በላቀ ሰብዕና ህብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል፡፡

"መመረቅ የስኬት ጫፍ ሳይሆን ረጅሙን የሕክምና ጉዞ የምትጀምሩበት የሕይወት ምዕራፍ በመሆኑ ሁልጊዜም ራሳችሁን በማብቃት ለህዝባችሁ መድህን ልትሆኑ ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

ምሩቃን ሕሙማንን በመርዳትና በመንከባከብ የሙያ ቃል ኪዳናችውን መጠበቅ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዶክተር አሸናፊ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም በርካታ የሕክምና ባለሙያዎችን በማፍራት አሻራውን አሳርፏል ብለዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልጃለም ጋሻው በበኩላቸው፣ በፈተና ውስጥ አልፈው ለምረቃ የበቁ የጤና ባለሙያዎች የሀገርና የወገን እንቁ ሀብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ላለፉት 100 ዓመታት በዘለቀው የሕክምና ትምህርት አገልግሎቱ ከሀገር አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ሀኪሞችን ማፍራቱን አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ ከ4 ሺህ በላይ የሕክምና ባለሙያዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ጠቁመው፣ ከማስተማር ሥራ በተጨማሪ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው የሕክምና ተማሪዎች መካከል በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁ ሦስት የሕክምና ዶክተሮች የወርቅ ሜዳሊያ እና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል፡፡

በምረቃ ሥነ ስርአቱ ላይ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስችለውን የዝግጅት ምዕራፍ እያጠናቀቀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም