ቀጥታ፡

የከተሞችን መሬት በአግባቡ ለማስተዳደርና ዘመናዊ አገልገሎት መስጠት የሚያስችል የመሬት ዲጂታል አድራሻ ተግባራዊ እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ የከተሞችን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለማስተዳደርና ዘመናዊ አገልገሎት መስጠት የሚያስችል የመሬት ዲጂታል አድራሻ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአዳማ ከተማ የመሬት ሃብትን በአግባቡ ማስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚያስችል የመሬት ዲጂታል አድራሻ ትግበራ ፕሮጀክት በዛሬው እለት ተመርቆ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን የዲጂታል ማፕ ርክክብም ተደርጓል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (/) በከተሞች የመሬት ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በከተሞች ዜጎች ለንብረታቸው ዋስትና እንዲያገኙ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመርና ስማርት መሰረተ ልማት ለማስፋፋት የመሬት ትራንስፎርሜሽንና ዲጂታል አድራሻ ትግበራ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በአዳማ ከተማ የመሬት ሃብትን በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል የመሬት ዲጂታል አድራሻ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል

በአዳማ ከተማ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመተግበርና የካዳስተር ስርዓት ወደ ስራ በማስገባት ቀዳሚና ብዙ ልምድ የተገኘበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በቀጣይም በከተሞች ቴክኖሎጂን የማስፋፋትና ወደ ስራ በማስገባት የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ፤ የአዳማ የዲጂታል መሬት ትራንስፎርሜሽን ስርዓት የከተማዋ ለዲጂታል ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበርም የመሬት ካዳስተር ስርዓት እውን እንዲሆን ማገዙን አንስተው በዛሬው እለት ተመርቆ ወደ ተግባር የገባው ፕሮጀክትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲህ አይነት ትግበራዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እቅድን ለማሳካት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (/) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ፕሮግራም 73 ከተሞች የመሬት ዲጂታል አድራሻ ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአዳማን ጨምሮ የዘጠኝ ከተሞች የዲጂታል አድራሻ ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸው 32 ከተሞች የዲጂታል አድራሻ ግንባታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት

የአዳማ ከተማ ዲጂታል አድራሻ የመሬት፣ የትራንስፖርት፣ የገቢ፣ የንግድና ሌሎች አገልግሎቶችን ዜጎች በተንቀሳቃሽ ስልክ ካሉበት ሆነው እንዲገለገሉ ያስችላል ብለዋል




የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የስማርት አዳማ ፕሮግራም በመቅረጽና በመተግበር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓትን ከማዘመን ባለፈ የሃብት ምዝበራ እንዳይከናወን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር፣ በመሬት አካባቢ የነበረውን ህገ ወጥ አሰራር የመከላከልና የገቢ አቅምን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም