በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃት እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃት እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ማሩ ጃኔ ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ማሩ ጃኔ እንደገለጹት፤ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በትኩረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ዜጎች በምርጫው ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ ፓርቲዎችም ማኒፌስቷቸውን እንዲያስተዋውቁና የምርጫውን ሕግና ደንብ አክብረው እንዲሰሩ ዘርፈ-ብዙ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሂደቱ ሰላማዊ እና የተሳለጠ እንዲሆን ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ከስድስተኛው ምርጫ አኳያ እያደረገ ያለው ጥረት ትልቅ እመርታ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ የመዲናዋ ነዋሪዎች የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ በተለያየ መንገድ ግንዛቤ በማስጨበጥ የተሳካ ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
ፓርቲዎች በምርጫው ሚናቸው እንዲጎለብት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር በምርጫ ሕጎች ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አክለዋል።
እንዲሁም ፓርቲዎች ማኒፌስቶአቸውን እንዲያስተዋውቁና አማራጮቻቸውን እንዲያቀርቡ ሥራዎች መሰራታቸውንም ጨምረው አስታውቀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን፤ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት ጠቅላላ ምርጫ መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።