ቀጥታ፡

ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ3 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል- ኮሚሽኑ

ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፡-የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተደረገ የተቀናጀ ጥረት በዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል።

በተለይ "ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026 ፎረም" የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ነው የገለጹት።

ይህም ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገር መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።

ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ኮሚሽኑ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በአሰራር ሥርአቱ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 372 አዳዲስ የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል ብለዋል።

ከዚህም 3 ነጥብ  52 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ16 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ በተጨማሪ የኢንቨስትመነት ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ተቀይረው ውጤት እንዲያመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። 

ባለፈው ዘጠኝ ወራት የተገኘው ውጤትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ጠንካራ ጥረት የመጣ መሆኑን ጠቁመው፣ ለቀጣይም ተቀናጅቶ በመስራት ተጨማሪ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። 


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ለሀገራዊ ዕድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርምን ተግባራዊ እያደረገ ነው።

በዚህም በክልሉ የግል ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የክልሉ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት አሰራርና አደረጃጀትን ከማጠናከር ባለፈ ፕሮጀከቶችን በመደገፉ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም አስታውቀዋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አፀደ አይዛ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል። 


 

በዚህም የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች በማድረግና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በማጠናከር አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ 1ሺህ 826 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በማኑፋክቸርንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ወደ ሥራ ገብተው ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም