ከኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የሚገኝ የቴክኖሎጂ እውቀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የሚገኝ የቴክኖሎጂ እውቀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል
ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቱን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክሕሎት እያሳደገ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ገለፀ።
በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ አቶ ደመላሽ በላይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የወጣቱን የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እየጨመረ ይገኛል።
በዋናነትም የወጣቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል።
ሥልጠናው በተለይ ወጣቱን በአንድሮይድ ማበልጸግ፣ በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ባለቤት እንዲሆን ማድረጉንም አብራርተዋል።
በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 30 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ደመላሽ፤ ሌሎች 10 ሺህ የሚደርሱት ደግሞ ሥልጠናውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሥልጠናውን ካጠናቀቁት መካከል 90 የሚሆኑት በቀሰሙት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት የራሳቸውን ሥራ መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ አየለ ፍሥሐ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ወጣቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው እያደረገ ነው።
ሥልጠናው በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከመደገፍ ባሻገር፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
በዘርፉ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት በሚደረገው ጥረትም በትብብር እየተሠራ መሆኑን አንስተው፣ ይህም የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሥልጠናውን ከወሰዱት ወጣቶች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪው ወጣት ዳዊት ዳምጠው፤ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሲሆን፣ የኮደርስ ሥልጠና በመውሰድ ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት ማዳበሩን ይናገራል።
በዚህም «አቢሲኒያ ዲጂታል» የተሰኘ ሲስተም በማበልጸግ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።
ሥልጠናው ዘመኑ የሚሻውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሀገርን፣ አካባቢንና ራስን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ፣ ሌሎች ወጣቶችም ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል መክሯል።
ወጣት መክሊት ጌቱ በበኩሏ፤ ሥልጠናው የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎቷን ለማሳደግ እንዳገዛት አንስታ፣ በቀጣይም በዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለመሰማራት ማቀዷን ተናግራለች።