ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት እያገዘ ነው

ዲላ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት እያገዘ መሆኑ ተገልጿል።


 

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ታምራት በየነ (ዶ/ር) እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እያገዘ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመተግበር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ይህም የልዩ ፍላጎት ትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ አቅም መፍጠሩን አመልክተዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር መምህርና ተመራማሪ አባቡ ተሾመ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት  የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ልዩ ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን የልማት ተሳትፎ እያሳደገ ነው።

በተለይም ተማሪዎቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚታገዙበትን አካታች ስርአት ለመዘርጋት ማስቻሉን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ ያደረገው ጽሁፍን ወደ ብሬል የሚቀይር ቴክኖሎጂ፣ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን የዲጂታል አቅም የማሳደግ ተግባር እንዲሁም የዲጂታል ቤተ መጽሐፍት አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማሳያነት ጠቅሰዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርትን ለማቀላጠፍ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያነሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሥነ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ወንድወሰን ገበያው (ዶ/ር) ናቸው።

ለዚህም የተማሪዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግና መሰረተ ልማትን ማሟላት ላይ ወሳኝ ሥራ መከናወኑን  ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው የዘረጋው የዲጂታል ተክኖሎጂ ትግበራ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው ያለው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል 3ኛ ዓመት ተማሪ ኢስማኤል ሽፍ ነው።

ዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ተክኖሎጂ ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች የሚያስተናግድ የመማር ማስተማር ምህዳር መፍጠሩ ለሌሎች አርአያ እንደሚሆንም ገልጿል።

ቴክኖሎጂው ትምህርታቸውን በቀላሉ እንዲከታተሉ በማድረግ ውጤታማ እንዳደረጋቸውም ጨምሮ ተናግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም