በምርጫው በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን- የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን- የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች
ሀዋሳ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ) :-በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን ሲሉ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል።
ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ሳይለዩ ባሉበት ሆነው በመመዝገብ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ምቹ መደላድል ተፈጥሯል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ በወሰዱት የመራጭነት ካርድ በመጠቀም በተለይ ለወጣቱ ተጠቃሚነት የሚሠራን ፓርቲ ለመምረጥ የድምፅ መስጫ ቀኑን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአፕላይድ ኬሚስትሪ እንዲሁም የገቨርናንስና ልማት ጥናት ትምህርት ክፍሎች የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የሆኑት ትንቢት ዳንኤል እና ሊዲያ በአካል፤ በጠቅላላ ምርጫው ለመሳተፍ የተመቻቸላቸው ዕድል በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የወሰዱትን የመራጭነት ካርድ ሳያባክኑ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ክርክር በንቃት እየተከታተሉ እንደሆነ የተናገሩት ተማሪዎቹ፤ ወጣቱን ማዕከል ያደረጉ የፖሊሲ አማራጮችን የሚያቀርብ ፓርቲን እንደሚመርጡም አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሲዳምኛ ቋንቋ ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ቡጤ በበኩሉ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለጠቅላላ ምርጫው ካርድ እንዲያወጡ በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ ለመራጭነት ብቁ የሚያደርገውን ካርድ መውሰዱን ተናግሯል።
ከትምህርት ገበታቸው ሳይለዩ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ እንዳስደሰተው ገልጾ፤ ካርዱን በመጠቀም ለሀገሪቱና ለዜጎች ቀጣይ ዕድገት ይበጃል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ገልጿል።
በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪና የተማሪዎች ሕብረት ፕሬዚዳንት ቢኒያም አየለ፤ ተማሪው በመጪው ምርጫ እንዲሳተፍ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመበት መሆኑን ገልጿል።
ይህም በተለይ ወጣቱ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብቱን እንዲጠቀም የሚያደርግና ትልቅ ኃላፊነት እንደተሰጠው የሚያመላክት መሆኑን ተናግሯል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ያሳዩትን ተነሳሽነት በምርጫው ዕለት በመድገም ይበጀናል ያሉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል።
የአንድ ሰው ድምፅ ዋጋ ያለው በመሆኑ፣ ያወጡትን ካርድ ሳያባክኑ በቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራ ፓርቲ የመምረጥ ዕድልና ኃላፊነትን መጠቀም እንደሚገባም አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅትም ለሀገርና ለሕዝብ መጻኢ ዕድገትና ለውጥ ይበጃል የሚለውን ለመምረጥ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።