አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ልማት ማከናወን የሁሉም ኢንዱስትሪያሊስቶች እሳቤ መሆን አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ልማት ማከናወን የሁሉም ኢንዱስትሪያሊስቶች እሳቤ መሆን አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ልማት ማከናወን የሁሉም ኢንዱስትሪያሊስቶች እሳቤ መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመዲናዋ ለመካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች ተስፋን፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ደግሞ የሥራ ዕድል የፈጠረውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ መርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሠራበት አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት የውሀ፣ መንገድ፣ የመብራትና ሌሎች መሠረተ ልማት ያልተገነባበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የገላን ጉራ አካባቢ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ዘመናዊ መንገድና ድልድይ፣ አረንጓዴ ቦታ፣ ለኑሮ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት የተሻለ ቦታ ሆኗል ብለዋል፡፡
ዓላማችን ከድህነት የተላቀቀች ኢትዮጵያን የሚፈጥር ትውልድ መገንባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተባባሪ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የልማት ሥራዎች አርሶ አደሮችን፣ ድሆችንና እጅ አጠሮችን የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ አርሶ አደሮችን በገዛ መሬታቸው ዘበኛ እያደረግን ልማት ማምጣት አንችልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዓለም የሚያደንቀው ልማትና ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተው፤ ከጊዜያዊ ፍላጎትና ስሜት በመውጣት በሥራ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ጊዜ ይፈልጋል፣ የተሟላ መሠረተ ልማት ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ያልነበራቸው የተደራጁ ወጣቶች ፓርክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ የውሀ ፓምፖች፣ የወርቅና የብሎኬት ማምረቻ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚመረቱበት የፋብሪካዎች ማምረቻ ፓርክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያሊስቶች የሚፈልቁበት ፓርክ በመሆኑ ኢንዱስትሪያችን በእኛ ሰዎች እንዲመራ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በተናጠል የሚሠራ ኢንዱስትሪ አያዋጣም፤ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ልማት ማከናወን የሁሉም ኢንዱስትሪያሊስቶች እሳቤ መሆን አለበት፡፡
ሁሉም ክልሎች ከገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትምህርት በመቅሰም ወጣቶችና አርሶ አደሮችን ያካተተ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመለወጥ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን በመጠበቅና በማልማት ዜጎችን ከሥራ አጥነት መታደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለውጥ የሚመጣው በሥራችንና በላባችን በመሆኑ እርስ በርስ በመዋደድና በመከባበር ሀገራችንን ማልማት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጀምረን ያላሳካነው አንድም ጉዳይ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌብነት በሥራ ላይ የሚበቅል አረም በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምዕራፍ አንድ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ የምረቃ መርሃ ግብር ተካሂዷል።