ቀጥታ፡

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ዋነኛ መገለጫ በመሆኑ ዜጎች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ዋነኛ መገለጫ በመሆኑ ዜጎች በሂደቱ እስካሁን ያደረጉትን የነቃ ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአንድ ሀገር የምርጫ ሂደት ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ገለልተኛና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ እና ወሳኝ ሚና አላቸው።

በምርጫ ወቅት ሊኖራቸው ከሚችለው ሚናዎች መካካል የመራጮች ትምህርት እና ግንዛቤ መፍጠር፣ የምርጫ ሂደቱን መታዘብ፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችና አካታችነትን ማረጋገጥ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን እንደገለጹት፤ ምርጫ፣ ሕዝብንና ሀገርን የሚያስተዳድር መንግሥት ወደ ሥልጣን የሚመጣበት ወሳኝ ሀገራዊ ክንውን ነው።

ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው በምርጫ ሂደት የሕዝብ ተሳትፎ ሲረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የዜጎች ሚና ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱ የምርጫው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ከጅማሬው ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

ከእነዚህም ዓበይት ክንውኖች መካከል ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማንቃት ሥራ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመራጮች ትምህርት እየሰጡ መሆኑንና ከ60 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሂደቱን ለመታዘብ ፈቃድ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበትና ስኬታማ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በምርጫው ሂደት የሕዝብ ተሳትፎ እንዲያድግ ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።




የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ከምርጫ ቦርድ በተሰጠው ፈቃድ የመራጮች ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ አባላት በምርጫ ታዛቢነት ለመሳተፍ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን፤ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት ጠቅላላ ምርጫ መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም