ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በጋና አክራ እየተካሄደ የሚገኘው 24ኛ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።

በወንዶች 20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር አትሌት ምስጋናው ዋቁማ አሸንፏል።

ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ በአፍሪካ ሻምፒዮና መድረክ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በማሸነፍ ክብሩን አስጠብቋል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አብዱልሰላም አብዱልዋሂብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስገኝቷል።


 

በሴቶች 20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ደግሞ አትሌት ውብአለም ሽጉጤ በቀዳሚነት አጠናቃ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

በዚሁ ውድድር ላይ የተካፈሉት አትሌት ሕይወት አምባው አራተኛ እንዲሁም አትሌት ማሬ ቢተው ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ ያገኘቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት አምስት ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሻምፒዮናው አምስት የወርቅ፣ አንድ የብር እና አምስት የነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

ሻምፒዮናው ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም