ቀጥታ፡

በኢሉአባቦር ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተዋል

መቱ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን በመጪው የክረምት ወቅት የሚተከሉ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

በፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በዘርፉ ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ፤ በዞኑ በልዩ ኢኒሼቲቭ እየተተገበሩ ከሚገኙ ዋና ዋና የግብርና ሥራዎች መካከል የፍራፍሬ ልማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለዜጎች የምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ አቅም እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።


 

በዞኑ በልዩ ትኩረት እየተዘጋጁ ከሚገኙት የፍራፍሬ ችግኞች መካከል የአቮካዶ፣ የሙዝ እና የፓፓያ ችግኞች ዋናዎቹ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ይህንኑ መልካም ጅምር ይበልጥ ለማጠናከርና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት፣ በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ45 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በችግኝ ዝግጅት ሂደቱም ምርታማነታቸው በተረጋገጠ ምርጥ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ኃላፊው አብራርተዋል።

በፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮችም ዘርፉ ለምግብ ዋስትናና ለገቢ ምንጫቸው ተጨማሪ አቅም እየሆናቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል መዘሚል አደም፣ "የምናመርተውን ፍራፍሬ ለአካባቢው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ከመሸጥ ባለፈ፣ ለሌሎች አርሶ አደሮችም የፍራፍሬ ችግኞችን እያቀረብን በዓመት ጥሩ ገቢ እያገኘንበት ነው'' ብለዋል።

አርሶ አደር ተካ መሐመድ እና ፈቀደ አረጋ፣ በግብርና ሥራቸው ውስጥ ለፍራፍሬ ልማት ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በተሻለ መልኩ የመልማት አቅማቸውን በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመጪው ክረምትም በተለይ የአቮካዶ ችግኞችን በስፋት ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም