የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018(ኢዜአ)፦ የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው ሲሉ የኪንግስ ኦፍ አባይ ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ሀገራዊ የሚዲያ ተቋማት የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ ሚዲያ የሀገርን ገጽታ በመገንባትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር በኩል እንደ ዋና መሣሪያ ያገለግላል።
ጋዜጠኞች ከሀገራዊ ጥቅም እና ከዜግነት ግዴታቸው አኳያ ገለልተኛ ሊሆኑ እንደማይችሉም አስገንዝበው የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የአንድ መንግሥት ፍላጎት ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር የሀገር ሕልውና ነው ብለዋል።
ስለሆነም የሚዲያ ተቋማት ሁልጊዜም ለሀገር ጥቅም የቀኑ መሆን ይኖርባቸዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኪንግስ ኦፍ አባይ ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ በነበረበት እ.ኤ.አ በ2019 የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን በሙሉ የተቀናጀ የሚዲያ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ይገልጻሉ።
በተለይም በግድቡ ዙሪያ በዓረብኛ ቋንቋ የሚነዛው የሐሰት ትርክት እጅግ አሳሳቢ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገሪቱን በተለያዩ መንገዶች ለማሳጣት የጀመሩትን የሚዲያ ዘመቻ ለመመከት ዋነኛ ግብ በማድረግ ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር የማይቀርብና በጋራ ሊቆሙለት የሚገባ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም የግል ፍላጎትንና ጥቅምን መሥዋዕት ማድረግን ጭምር ይጠይቃል ነው ያሉት።
ብሔራዊ ጥቅሞችን በግልጽ መለየት፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ እና ከግለኝነት በጸዳ መልኩ ለሀገር ዘብ መቆምን ይጠይቃል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የባሕር በር የኢትዮጵያ ቀዳሚ ብሔራዊ ጥቅም መሆኑን ጠቅሰው፤ በአስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ኢትዮጵያዊ ሊኖር እንደማይገባ ተናግረዋል።
አንድ ጋዜጠኛ ሙያዊ ግዴታውን ከሀገራዊ ወገንተኝነት ጋር በማጣመር የሀገርን ሕልውና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል።
በዲጂታልም ሆነ በዋናው የሚዲያ ተቋማት የሚሰሩ ጋዜጠኞች በሀገር ጥቅም ላይ ተቆርቋሪነትን ሊያንጸባርቁ እንደሚገባም መክረዋል።