ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ36 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ45 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት ያልቻለው ወልዋሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ፈቀቅ እንዲል ያደርገዋል።

በ31ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን 3 ለ 1 የረታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ሃዋሳ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ በ44 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

አርባምንጭ ከተማ በ28 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ በ31ኛ ሳምንት በወላይታ ድቻ የ3 ለ 2 ሽንፈት አስተናግዷል።

ሃዋሳ ከተማ ከድል ጋር ለመታረቅ፣ አርባምንጭ ከተማ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ሶስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ፍልሚያ ትኩረትን ስቧል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ፋሲል ከነማ በ43 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ፋሲል ከነማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።

በ31ኛ ሳምንት ምድረ ገነት ሽሬን 4 ለ 0 በመርታት ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ሶስት ነጥብ ያገኘው አዳማ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም