ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሞሮኮ አቻውን ይገጥማል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

በምድብ አንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከአዘጋጇ ሞሮኮ ጋር ምሽት አራት ሰዓት ላይ በመሐመድ ስድስተኛ እግር ኳስ ኮምፕሌክስ ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታው ከግብጽ ጋር ያለ ግብ አቻ በመውጣት አንድ ነጥብ አግኝቷል።
ቡድኑ በጨዋታው ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርጓል።

አዘጋጇ ሞሮኮ በመጀመሪያ ጨዋታ ቱኒዚያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ምድቡን እየመራች ነው።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመዋር ቡድን ከምድቡ ለማለፍ እና በኳታር ለሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማለፍ ህልሙን ለማሳካት ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል።

የአጥቂ መስመሩ የሚፈጠሩ የግብ ዕድሎችን ወደ ውጤት የመቀየር አቅሙን ማሳደግ ይኖርበታል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን በመሐመድ ስድስተኛ እግር ኳስ አካዳሚ ማድረጉንና ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚሁ ምድብ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ቱኒዚያ ከግብጽ በመሐመድ ስድስተኛ እግር ኳስ ኮምፕሌክስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም