የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ማን ያነሳል? ቼልሲ ወይስ ማንችስተር ሲቲ? - ኢዜአ አማርኛ
የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ማን ያነሳል? ቼልሲ ወይስ ማንችስተር ሲቲ?
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2018 (ኢዜአ)፦ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ለማንሳት ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ 90 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዌምብሌይ ስታዲየም ይካሄዳል።
ቼልሲ ሊድስ ዩናይትድን እንዲሁም ማንችስተር ሲቲ ሳውዝሃምተንን በማሸነፍ ለፍጻሜው ማለፋቸው የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፕ ታሪካቸው ለ10ኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን፣ ቀደም ባሉት ዘጠኝ ግንኙነቶች ማንችስተር ሲቲ ስድስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
በአንጻሩ ቼልሲ በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
በዘጠኙ ጨዋታዎች ላይ ማንችስተር ሲቲ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር ቼልሲ ዘጠኝ ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተገናኙት እ.አ.አ በ1915 በሶስተኛ ዙር ላይ ሲሆን ቼልሲ 1 ለ 0 አሸንፏል።
እ.አ.አ በ2024 ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ 1 ለ 0 በመርታት ለፍፃሜው አልፏል።
ቼልሲ ለኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ሲያልፍ ይህ ለ17ኛ ጊዜው ነው። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ እስከ አሁን ስምንት ጊዜ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችሏል።
ማንችስተር ሲቲ ለ14ኛ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰ ሲሆን፣ እስካሁን ባደረጋቸው የፍጻሜ ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ታሪካዊውን ዋንጫ ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ ፣ ብርቱ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቼልሲ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ካነሳ ለዩሮፓ ሊግ ማለፉን ያረጋግጣል።
የ40 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
154 ዓመታትን ያስቆጠረው ኤፍኤ ካፕ የዓለማችን እጅግ አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድርነው።