በክልሉ በበልግ አዝመራ በሆርቲካልቸር እና በዋና ዋና ሰብሎች ከ575 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በበልግ አዝመራ በሆርቲካልቸር እና በዋና ዋና ሰብሎች ከ575 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለምቷል
ቦንጋ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተያዘው የበልግ አዝመራ በሆርቲካልቸር እና በዋና ዋና ሰብሎች ከ575 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው የበልግ እርሻ አፈፃፀምን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በዘንድሮ የበልግ አዝመራ የዜሮ ግብ አቅጣጫን በመከተል ከዚህ ቀደም የማይታረሱ ማሳዎች ጭምር እንዲታረሱ በተደረገ ርብርብ 575 ሺህ 160 ሄክታር ማሳ በሆርቲካልቸር እና በዋና ዋና ሰብሎች መልማቱን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በበልግ የለማው መሬት ከአምና በ50 ሺህ ሄክታር ጭማሪ እንዳለው ገልጸው፤ በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ከለመው መሬት 16 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ መተጣሉን አንስተዋል።
በእስካሁኑ ሂደት 422 ሺህ 87 ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ ከዚህም ውስጥ 129 ሺህ 200 ሄክታሩ በክላስተር የለማ ነው ብለዋል።
የሚታረስ ማሳን መጠን ከማሳደግ ባለፈ 46 ሺህ 200 ሄክታር በትራክተር መታረሱን ያነሱት አቶ ማስረሻ፣ ይህም አርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን እርሻን ለመጠቀም ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
በክልሉ ለኤክስፖርት ምርቶች በተሰጠ ልዩ ትኩረትም ከ42 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በቅባት እህሎች፣ በማሾ፣ በሰሊጥ፣ በቦሎቂና በሌሎች ሰብሎች መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ፍራፍሬ ሌላው ትኩረት የተሰጠው የሆርቲካልቸር ሰብል መሆኑን ገልጸው፤ ችግኞችን አዘጋጅቶ ከመትከል ባለፈ ምርታማነትን ለማሳደግም ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ፣ በበልግ ወቅት 50 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 50 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
እስካሁንም 23 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፣ በፍራፍሬ ልማቱ ከነባር ማሳ 19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።
የእንሰት ልማትን ለማስፋት በተሰጠው ልዩ ትኩረት 95 ነጥብ 6 ሚሊዮን የእንሰት ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ግብአት አጠቃቀምን ለማሳደግ በተሰጠ ትኩረትም መሻሻል እንዳለ ገልጸው፣ በበልግ ወቅት 159 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንዲሁም 86 ሺህ 205 ኩንታል ዩሪያና ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።
ከበልግ የእርሻ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ከ70 ሚሊዮን ኩንታል በለይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ የተያዘ ሲሆን፣ ይህን ለማሳካት የአረም ቁጥጥርና የተባይ አሰሳ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።