ለሀገር ዘላቂ ልማት የሚተጋ መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ ማፍራት ላይ ሁላችንም በትኩረት ልንሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ዘላቂ ልማት የሚተጋ መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ ማፍራት ላይ ሁላችንም በትኩረት ልንሰራ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦የሀገርን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚተጋ መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ ማፍራት ላይ ሁላችንም በትኩረት ልንሰራ ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለፁ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የቤተሰብ ቀን "በመልካም ቤተሰብ፣ መልካም ትውልድ፣ለፀና ሀገር!!" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ኹነቶች ተከብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ቤተሰብ መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ የሚፈራበት ትልቅ ተቋም ነው።
መልካም ቤተሰብ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት አቅም የሚፈጥር ትውልድ ለመፍጠር መሰረት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ኢትዮጵያዊ ባህልን እና እሴትን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻግር አርዓያ ቤተሰብን በገነባን ቁጥር በምንፈልገው ልክ በመልካም ስብዕና የታነጸ ዜጋን ማፍራት እንችላለን ብለዋል።
ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው የቤተሰብን ማህበራዊ ደኅንነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ሁላችንም የማህበረሰብ ክፍሎች የራሳችንን ሚና በአግባቡ ስንወጣ ነው ያሉት።
ዜጎች ኢትዮጵያዊ ቤተሰባዊነታችንን በማጠናከር ለሀገር ልማታዊ እድገት የሚሰራ መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ ማፍራት ላይ ሁላችንም በትኩረት ልንሰራ የሚገባን ወቅት ላይ ነን ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።
በቤተሰብ ውስጥ ቅርብ ውይይት በማድረግ፣ ለልጆች ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እንዲገነዘቡ በማድረግና ስራ ወዳድነትን በማስተማር ጠንካራ ሀገር በመገንባት ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አሁን ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን በመሆኑ ቤተሰብ ልጆቻቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለበጎ ዓላማ እንዲያውሉ በመስራት ለኢትዮጵያዊ ቤተሰባዊነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሻለች ኢትጵያን ለመገንባት የቤተሰብ ደኅንነትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን በተጠናከረ መንገድ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አልባስጥሮስ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ እና የሴቶች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ኑኑ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ ቤተሰቦች መልካም ስብዕናን በመላበስ ለምናፈራቸውን ልጆች አርዓያ ልንሆን ይገባናል ብለዋል።
በተለይም ልጆች በማይጠቅማቸው ነገሮች ጊዚያቸውን እንዳያባክኑ ከልጆቻችንን ጋር በቅርበት መወያየት ሀሳባቸውን መስማት ይገባናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ትውልዱን በማነጽ ረገድ የሀገሪቱን ባህል የሚያከብሩ ትውልዶችን የመፍጠር ስራ መስራት ሀገራዊ ግዴታችን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ታዬ ሰንበታ ናቸው።
አባቶቻችን አሁን ላለነው ማህበረሰብ ውብ ባህልና እሴት አውርሰውን አልፈዋል ያሉት አቶ ታዬ ይህን ድንቅ ሀብት ለትውልዱ ማውረስ ከእኛ ከቤተሰቦች ይጠበቃል ብለዋል።