ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ቅርሶች በአዲስ አበባና ጎንደር ከተሞች ለህዝብ ዕይታ ይቀርባሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ቅርሶች በአዲስ አበባና ጎንደር ከተሞች ለህዝብ ዕይታ ይቀርባሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተዘርፈው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ቅርሶች በአዲስ አበባ ብሔራዊ ሙዚየምና በጎንደር አፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት ግቢ በሚዘጋጅ ጊዜያዊ ኤግዚቢሽን ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
በተለያየ ጊዜ ከሀገር ወጥተው በእንግሊዝ የነበሩ ቅርሶች በመንግስት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የርክክብ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።
የእንግሊዝ ንጉስ ቤተሰብ ሙዚየም ኃላፊ ኮሎኔል ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) እና ማህበራዊ አንትሮፖሎጂስት፣ ተመራማሪና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አስረክበዋል።
በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ለረጅም ጊዜ በእንግሊዝ የቆዩ የአፄ ቴዎድሮስ የእጃቸው የወርቅ አምባር፣ የፀጉራቸው ቁንዳላ (ትንሽ ዘለላ) እና የሸማ ሸሚዝ ቁራጭ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት የነበሩት የእቴጌ ጥሩ ወርቅ ውቤ የጸጉር ጌጥ (ወለባ)፣ ታሪካዊ ጋሻ፣ የመጠጫ ዋንጫዎች እና የተለያዩ ስዕሎች ተካተዋል።
በዚሁ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ አፄ ቴዎድሮስ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመቅዳላ ጦርነት ወቅትም የአፄ ቴዎድሮስ የንግስና መገልገያ፣ የፀጉር ቁንዳላና ጌጣጌጥን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች መዘረፋቸውን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ የተደረጉ ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ውይይትና ስምምነቶችን ተከትሎም ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።
ከ158 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ፣ የልብስ ቁራጮችና የወርቅ አምባር ቅርሶች በአዲስ አበባና ጎንደር ከተሞች ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
ቅርሶቹም በአዲስ አበባ በብሔራዊ ሙዝየምና በጎንደር ደግሞ በአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ቅጥር ግቢ በሚዘጋጅ ጊዜያዊ ኤግዚቢሽን ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።
የማህበራዊ አንትሮፖሎጂስትና የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ቅርሶች ይዘትና ታሪካዊ እውነት በጥልቅ ምርምር የተረጋገጠ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት የማስመለስ ሥራም የታሪክን ህያውነት በማረጋገጥ ሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የእንግሊዝ ንጉስ ቤተሰብ ሙዚየም ኃላፊ ኮሎኔል ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው ቅርሶች መመለስ የሀገራቱን ወዳጅነት በትግባር የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሙዚየምና ቅርስ ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ አሰፌ፤ የኢትዮጵያ ቅርሶች መመለስ ትውልድ ለሀገርን የተከፈለን ውድ ዋጋና ጀግንነት እንዲገነዘብ ያስቻላል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በተቋቋመው ሙዝየም የተሰነዱ ቅርሶችንና ወታደራዊ ታሪኮችን ህብረተሰቡ በመጎብኘት የተከፈሉ ጀግንነቶችን መሆኑን ገልጸዋል።