ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሮበርት አፍሪዬን (ዶ/ር) አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሮበርት አፍሪዬን (ዶ/ር) አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሮበርት አፍሪዬን(ዶ/ር) አሰናበቱ፡፡
ተሰናባቹ አምባሳደር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታና ስለሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት በተመለከተ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የነበረኝ ቆይታ እጅግ ድንቅ ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ሁለተኛ ቤቴ እንደመጣሁ ነው የተሰማኝ በማለት ገልጸዋል።
በቆይታቸውም በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ዘርፍ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ እጅግ ፍሬያማና ስኬታማ ጊዜ እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡
የተያዘው የግንቦት ወር በኢትዮጵያ “የጋና ወር” ተብሎ እየተከበረ መሆኑን ገልጸው፤ በዝግጅቱ በሁለቱ ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ መካከል ውይይት፣ የልምድ ልውውጥ እና ትስስር ተፈጥረውበታል ብለዋል፡፡
ጋና አፍሪካውያን የካሳ ፍትህ እንዲያገኙ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበውን ታሪካዊ የውሳኔ ሃሳብ በግንባር ቀደምትነት ስትመራ ኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ መስጠቷን ተናግረዋል፡፡
ውሳኔው ከ80 ዓመታት በኋላ በጋራ የጸደቀ ሲሆን፤ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና ከመጀመሪያው የጋና ፕሬዝዳንት ዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ ጀምሮ የነበረውን የፓን-አፍሪካኒዝም እና የአፍሪካ አንድነት አጋርነት በተግባር ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታላቅ ለውጥ እና የፓን-አፍሪካኒዝም ተምሳሌት መሆኗን በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አክራ የሚያደርገውን በረራ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መጀመር ለሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ትልቅ ድልድይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ጋና ከኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቆዳ ውጤቶችን እና ቡና በቀጥታ መግዛት ያስችላታል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከጋና ጥራት ያላቸው የካካዋ፣ የቾኮሌት፣ የካሪቴ ቅቤ (Shea Butter)፣ የአፍሪካ አልባሳት እና ዲዛይኖችን መግዛት እንደሚያስችላትም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን አጠቃላይ የእድገት ጉዞ ያደነቁት አምባሳደሩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ዘመናዊ እና ውብ ሆና መለወጧን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ "የእናንተ ስኬት የእኛ ስኬት ነው፤ የእኛም ስኬት የእናንተ ስኬት ነው" ብለዋል፡፡