ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ አስደናቂ የልማት ስኬት የመደመር ዕሳቤ ለትውልድ የሚሻገር ጥበብ የተገለጠባትን ከተማ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ አስደናቂ የልማት ስኬት የመደመር ዕሳቤ ለትውልድ የሚሻገር ጥበብ የተገለጠባትን ከተማ መፍጠሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባን የለውጥ ጉዞ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተጻፈውን "THE REMAKING OF ADDIS ABABA" የተሰኘውን መፅሐፍ መርቀዋል።


 

በዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተሰነደው መፅሐፍ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበችውን አስደናቂ ዕድገት ለታሪክ፣ ለመልካም ተሞክሮ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲያገለግል የተሰናዳ ነው።

በዚሁ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በሀገራዊ ለውጡ ስምንት ዓመታት ውስጥ በመዲናዋ የመጣው አስደናቂ ለውጥ የከተማዋን የዕድገት ህልም ወደ ተግባር የለወጠ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገር በቀል የመደመር ፍልስፍናም አዲስ አበባን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውበትና ፀዳል ያጎናፀፉ የልማት ስኬቶች ባለቤት ማድረጉን ገልጸዋል።

የመደመር ፍልስፍና የተበታተኑ አቅሞችን አሰባስቦ በማስተባበር ስብራትን የሚጠግኑና ጉድለትን የሚሞሉ አዳዲስ ዕሴቶችን ፈጥሮ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ጥበብ የተተረጎመበት ዕሳቤ መሆኑን አስረድተዋል።

በዕሳቤው መነሻነት በአዲስ አበባ የተገኙ የልማት ስኬቶችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን የሚጠግን አንፀባራቂ ድል የተገኘባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ስኬታማ የለውጥ ጉዞም የህዝብና መንግስትን መተማመንን በማፅናት ደልድይ የገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የልማት ሥራዎቹ ህዝቡ በጉልበቱና በገንዘቡ ያደረገው ድጋፍ የአዲስ አበባን ገፅታ ከመቀየር ባሻገር የአብሮነትና የትብብር መንፈስ የጎለበተበትን ወሳኝ ዕድል እንደፈጠረ አንስተዋል።


 

በመጽሐፉ የተከተቡ መረጃዎችም የአዲስ አበባን ለውጥ በግልፅ የሚናገሩ፣ የተከፈለውን ዋጋና የወገንን ታሪክ ለመቀየር የተደረገውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ሕያው ምስክሮች ናቸው ብለዋል።

መጽሐፉ የእያንዳንዳቸውን ጥረትና ድካም የሚዘክር በመሆኑ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲያነቡትና ለሌሎች እንዲያጋሩት አሳስበዋል።

መጪው ትውልድ ከዚህ ተሞክሮ ተምሮ የተሻለች ሀገርና ከተማ እንዲገነባ መነሻ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀው አዲስ አበባ ወደፊትም አዲስ ታሪክ መጻፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም