ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ለውጥ በጠራ ራዕይ፣ በበሳል አመራር እና በዜጎች ፅኑ ትጋት የተገኘ ስኬት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ ለውጥ በጠራ ራዕይ፣ በበሳል አመራር እና በዜጎች ፅኑ ትጋት የተገኘ ስኬት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች የአዲስ አበባን የለውጥ ጉዞ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተጻፈውን "THE REMAKING OF ADDIS ABABA" የተሰኘውን መፅሐፍ መርቀዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መጽሐፉ የአዲስ አበባን መልክ መቀየር ብቻ ሳይሆን፤ የአንድን ትውልድ የማይበገር ወኔ፣ የታሪክ ስሪት እና የነገን ተስፋ የሚተርክ ህያው ሰነድ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ማንም ባልጠበቀው ፍጥነት እና ባልገመተው ጥራት ተለውጣለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ስሟ አበባ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ከተሞች የብልፅግና ተምሳሌት የለውጥ መስታወት መሆኗን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን የመቀየር ጉዞ የሀሳብ ብቻ ሳይሆን የትልቅ ራዕይ፣ የጠንካራ አመራር እና የጽናት ውጤት መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

ከተማዋን የማዘመን ስራ ሲጀመር በርካታ ተግዳሮቶች እና ስር የሰደዱ ዘርፈ ብዙ እንቅፋቶች እንደነበሩ አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት በሳልና አርቆ አሳቢ አመራር፣ በከተማዋ አመራር እና በነዋሪዎቿ የቀን ከሌሊት ትጋት ሩቅ ይመስል የነበረው ራዕይ ዛሬ እውን ሆኗል ብለዋል፡፡


 

"THE REMAKING OF ADDIS ABABA" መጽሐፍ ይህንን የአመራር ጥበብ፣ የትጋት ፍሬ እና የዜጎችን የልፋት ውጤት ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

ለውጥ ያለ መስዋዕትነት አይመጣም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መጽሐፉ በልማት ሂደት ውስጥ ሌሊትና ቀን የደከሙትን፣ በዝናብና ፀሐይ ሳይበገሩ መዲናዋን ለማሳመር ላባቸውን ያፈሰሱ ዜጎችን ድካምና ፍሬ በታሪክ መዝገብ ላይ አስፍሯል ብለዋል፡፡

የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ለቀጣዩ ትውልድ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ጠንካራ የስራ ባህልን ማሳየት መሆኑን ጠቅሰው፤ መጽሐፉ ለዛሬና ለነገ ትውልድ የትጋትን ኃይልና የማይቻል ነገር እንደሌለ አስተማሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተከናወነው ሥራ የለውጥ ችቦ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ታላቅ ቅርስ መሆኑን በመግለጽ፤ ሌሎችም ምሁራን የኢትዮጵያን ዕምቅ ሀብትና ለውጥ በአካል በመመልከት እንዲጽፉ  ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም