ቀጥታ፡

ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቷቸዋል

 አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተካሄደዋል።
 
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
 
ፍፁም ፍትዓለው እና አንተነህ ተፈራ ግቦቹን አስቆጥረዋል። 
 
በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ባህር ዳር ከተማ በ44 ነጥብ ደረጃውን ከ9ኛ ወደ 6ኛ ከፍ አድርጓል።
 
በውድድር ዓመቱ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ34 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።




 በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሸገር ከተማን 2 ለ 1 ረቷል።

 አዲስ ግደይ እና ናትናኤል ዳንኤል ለንግድ ባንክ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
  
 ቢንያም ፍቅሩ የሸገር ከተማን የማስተዛዘኝ ግብ አስቆጥሯል።
 
 በውድድር ዓመቱ 10ኛ ድሉን ያገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ41 ነጥብ ከነበረበት 14ኛ ደረጃ ወደ 11ኛ ከፍ ብሏል።
 
 በሊጉ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሸገር ከተማ ደግሞ በ40 ነጥብ ከ12ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ወርዷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾቹ አዲስ ግደይ እና ናትናኤል ዳንኤል በሊጉ ያስቆጠሩትን የግብ መጠን በተመሳሳይ 11 በማድረስ፣ በ14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደረጃ እየመራ የሚገኘውን የሲዳማ ቡናውን አቤል ያለውን ይከተላሉ።
 
 ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ የ32ኛ ሳምንት ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ መድን አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም