ቀጥታ፡

በአድማ መከላከልና መቆጣጠር ሥልጠና ያገኘነው ዕውቀት የሚሰጠንን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት አቅም የሚፈጥር ነው -የፌዴራል ፖሊስ አባላት

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በአድማ መከላከልና መቆጣጠር ሥልጠና ያገኘነው ዕውቀት የሚሰጠንን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ትልቅ አቅም የሚፈጥርልን ነው ሲሉ በዘመናዊ አድማ መከላከል የሰለጠኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ገለፁ።

የአድማ መከላከል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ሹሙዬ ነጋ በበኩላቸው አድማ መከላከል ሃይሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመታጠቁ ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል አቅም ማካበቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዘመናዊ አድማ መከላከልና መቆጣጠር የሰለጠኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ትናንት አስመርቋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወሰዱት ስልጠና ወቅቱን ታሳቢ ያደረገና ቀጣይ በሚኖራቸው የስራ ስምሪት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

በዚህም የተለያየ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መውሰዳቸወን ገልፀው፤ መጪው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የድርሻቸውን ለመወጣት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በፌዴራል ፖሊስ የአድማ መከላከል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ሹሙዬ ነጋ፤ አድማ መከላከል ሃይሉ የተሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል አቅም ማካበታቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።


 

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና ሳጅን መሃሪ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የወሰዱት ስልጠና የተለያዩ ዘመናዊ መሳርያዎችን በመጠቀም አድማን መከላከል የሚያስችል አቅምና ክህሎት የሚያሳድግ መሆኑን ገልፀዋል።

ስልጠናው ወደፊት ለሚያከናውኗቸው ሀገራዊ ተልዕኮዎች በበለጠ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ዋና ሳጅን መሃሪ፤ በቀጣይ የሚደረገውን ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።


 

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ሳጅን እመቤት ካስዬ፤ የወሰዱት ስልጠና አድማ ጉዳት ሳያደርስ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መከላከል የሚያስችል መሆኑ ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሆኖ እንዲከናወን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም