ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የምርምር ስራዎች እያከናወነ ነው

አዳማ፣ ግንቦት 7/2018(ኢዜአ)፦ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

ችግር ፈቺ ምርምሮች የሚቀርቡበት 4ኛው ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።   


 

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ፤ ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እያከናወነ ካለው የመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ ዘርፈ ብዙ የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ከአካባቢና ተፈጥሮ ጋር የሚስማማ የተቀናጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማትና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሀገሪቱ እያደረገች ያለችውን ጥረት በሙያ፣ በዕውቀትና በምርምር እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።   

አሰራርና አገልግሎትን ለማዘመን፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በልማት ፕሮጀክቶች ጭምር በማማከር እያገዘ እንደሚገኝም ተናግረዋል።   

በአካባቢ ጥበቃና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ በአፈር ለምነት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትና ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የመፍትሔ ሐሳቦች እየጠቆመ መሆኑንም ገልጸዋል።   

ዩኒቨርሲቲው አዳማ ከተማን ጨምሮ በቢሾፍቱና በሸገር ከተማ እየተገነቡ ያሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂና አገልግሎቶች የማዘመን ስራን በሙያ፣ በዕውቀትና በምርምር እያገዘ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።   

ዩኒቨርሲቲው የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምርምር ፓርክ በመገንባት፣ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የምርምር ቴክኖሎጂ፣ በላቦራቶሪዎችና በመሳሪያዎች እያደራጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።   


 

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መስፍን ነገዎ እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ የጀመረችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር መደገፍ አለባቸው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምር የተደገፉ አመላካች መፍትሄዎችን በማቅረብ ለአሰራር፣ ለስትራቴጂና ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ማገዝ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።   

በተለይ መንግሥት አገልግሎቶችን ለማዘመን የጀመረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሳካ ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።   

በኢንዱስትሪ ትስስር፣ በኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ልማት፣ በማህበረሰብ አገልግሎቶች እንዲሁም በምርምር ፓርክና በልህቀት ማዕከላት በማደራጀት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሻገር እያደረገ ያለው ጉዞ የሚደነቅ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።   

በተለይ የዲጂታል አገልግሎትን ጨምሮ የስማርት መሰረተ ልማት ዝርጋታን በሳይንሳዊ ምርምር በመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።   

በዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት መምህር ዶክተር ኬይረዲን ተማም እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ የተጀመሩ የስማርት መሰረተ ልማት ፕሮግራሞችን በምርምር ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።   


 

አካታችና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የአየር ንብረት ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ስማርት መሰረተ ልማት ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘመናዊ መሰረተ ልማት መገንባት ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።   

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ተመራማሪዎችና ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም