በመጪው ክረምት አብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ክረምት አብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ
አዳማ፣ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በመጪው ክረምት አብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመጪው የክረምት ወቅት የሚኖረውን የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ አድርጓል።
በትንበያው መሠረት በሀገሪቱ በምዕራብ አጋማሽ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሰሜን ምስራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖር ታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የክረምት ወራት ለሰሜን፣ ለምስራቅ፣ ለመካከለኛው፣ ለሰሜን ምዕራብና ለምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዋና የዝናብ ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል።
በዝናብ ስርጭቱ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ መተንበዩን ገልጸዋል።
መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚያገኙት ደግሞ ደቡብና ምስራቅ ትግራይ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ የአፋር ክልል ዞኖች፣ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም የመካከለኛውና የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መደበኛና በጥቂት ስፍራዎች ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚያገኙት አካባቢዎች ደግሞ የመካከለኛውና የምዕራብ አማራ ዞኖች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው ክረምት በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀድሞ የሚጀምር ሲሆን፣ እስከ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ሳምንት ድረስ ሁሉንም የሀገሪቱን አካባቢዎች እንደሚያዳርስ ገልጸዋል።
የክረምቱ ዝናብ አወጣጥን በተመለከተም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የሚዘገይ ሲሆን፣ በአብዛኞቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ግን ቀድሞ እንደሚወጣ ትንበያው አመልክቷል ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ አካባቢዎች ተደጋጋሚና ከባድ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት፣ በማሳ ላይ ውሃ መተኛትና ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችልም አንስተዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን በማጽዳትና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ፣ የግብርና ስራዎችንና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ከትንበያው ጋር በማጣጣም እንዲያከናውን ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።