ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ የልማት ፕሮጀክቶችን አቅዶ የተገበረ ፓርቲ ነው

ነገሌ ቦረና/አምቦ ፤ግንቦት7/2018(ኢዜአ)፡-ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ የልማት ፕሮጀክቶችን አቅዶ የተገበረ ፓርቲ መሆኑን በፓርቲው የቅስቀሳ መድረክ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች እና አመራሮች ገለጹ። 

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ቦረና ዞን ነገሌ ቦረና ከተማ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የእጩዎች ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሂዷል።   

በነገሌ ቦረና ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ መድረክ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ የለውጡ ዓመታት የአርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።   


 

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኮንሶሌ ተኑ፤ ቀደም ሲል ለዘመናት የነበረው የዝናብ ጥገኝነትና ኋላቀር የግብርና አሠራር አካባቢውን ለድህነት ዳርጎት እንደነበር አስታውሰዋል።   

ይሁን እንጂ የለውጡ መንግሥት የተገበራቸው የበጋ መስኖ፣ የአረንጓዴ አሻራና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ድርቅን በራስ አቅም ለመቋቋም ትልቅ ተስፋ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ሹኬ ጎዳና የመጠጥ ውሃ፣ የመንገድና የመስኖ መሠረተ ልማቶች የአርብቶ አደሩን የኑሮ ጫና ያቀለሉና ለሥራ የሚያነሳሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  


 

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሥጋ፣ የወተት፣ የእንቁላልና የማር ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሾባ ዳለቻ ናቸው።   


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ፈስሶባቸው የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም አብዲ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ ድምፁን በመስጠት የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።   


 

በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በተካሄደ የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ የተገኙት እጩ ተረፈ በዳዳ (ዶ/ር) ፓርቲው የሕዝብን አንድነትና እኩልነት በማስከበር ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።   

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ እንደበቃ ሁሉ፣ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ ሕዝቡ ለብልፅግና ፓርቲ ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።   

በብልፅግና ፓርቲ የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፤ ፓርቲው የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ይገኛል ብለዋል።   

የልማት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍና ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሉሌሳ ናቸው።   


 

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አቶ እንዳሉ ረጋሳና ወይዘሮ አለም ዋሪዮ፤ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የሚያስቀጥል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም