ቀጥታ፡

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው

አሶሳ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የማህበረሰቡን ችግሮች በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም አስታወቁ።

ዩኒቨርሲቲው 11ኛውን ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ እያካሄደ ነው።

በኮንፍረንሱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ከማል አብዱራሂም (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ በተሰጠው የአፕላይድ ሳይንስ የትምህርት መስክ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። 


 

በዚህም በግብርና፣ በማዕድን እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የምርምር ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይም በግብርናው ዘርፍ ያከናወናቸው የምርምር ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎች፣ በማንጎ በሽታ መከላከል እንዲሁም በቀርከሃ ሀብት ልማት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

እነዚህ የምርምር ውጤቶች በቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ እንዲወርዱ በመደረጉም በአካባቢው ምርትና ምርታማነት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠራቸውን አብራርተዋል።


 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሁሉም ዘርፍ የሚያከናውኗቸው የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ፣ ለሀገራዊ የፖሊሲ ቀረጻ በግብዓትነት ማገልገል እንደሚገባቸውም ዶክተር ከማል ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዑመር ሸሪፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ ለተመራማሪዎች አቅም ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል። 


 

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ የምርምር ስራዎቹ ተመራማሪዎች በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲያዳብሩና በዓለም አቀፍ የሳይንስ መድረኮች ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ሰፊ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምርምር ኮንፈረንስ ላይ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ቁልፍ ዘርፎች ላይ የተከናወኑ የምርምር ስራዎች ለውይይት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። 

በምርምር ውጤቶቹ ላይ የሚደረገው ጥልቅ ውይይትም በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደቱ ይበልጥ መጠናከር እንደ አቅጣጫ የሚያገለግሉ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም