ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የባህል ሳምንት የሕዝቦችን አብሮነትና የባህል ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መድረክ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ የባህል ሳምንት የሕዝቦችን ኅብረብሔራዊ አንድነት፣ አብሮነትና የባህል ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መድረክ መሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ።  

"የባህል ልማት ለኅብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ ከትናንት ጀምሮ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየው ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ሳምንት በአዲስ አበባ መከፈቱ ይታወቃል።  

በአዲስ አበባ የተከፈተው የባህል ሳምንት የኢትዮጵያን ውብ የባህል ትርኢቶች ለዓለም ከማሳየት ባለፈ፣ በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርን በመገንባት የጋራ እሴቶችን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የመጡ የባህል ቡድን ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ መድረኩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ የባህል ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ሰፊ ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የባህል ቡድንን በመወከል የመጣው ስንታየሁ ደለለ እንደገለጸው፤ የባህል ሳምንቱ ሀገራዊ አንድነትን የሚያመጣና እርስ በርስ ያለንን ማኅበራዊ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብሏል። 

የትግራይ የባህል ቡድንን ወክላ የመጣችው አደይ ገብረሚካኤል በበኩሏ፤ እንደዚህ ዓይነት ፌስቲቫሎች መዘጋጀታቸው ባህላችንን በጋራ ለማሳደግ እና ሕዝቦች እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ የሚያስችል ነው ስትል ገልጻለች።

በተመሳሳይ የጋምቤላ የባህል ቡድን ተወካይ የሆነው ኢዮኤል ኤናው መድረኩ ኅብረብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክርና ጠንካራ ሀገራዊ ትስስርን የሚፈጥር ነው ሲል  ጠቅሷል፡፡ 

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህል ቡድን የመጣው ይመር ባይላ  በሰጠው አስተያየትም፤ የባህል ሳምንቱ አንዱ የሌላውን ባህል፣ ወግና ሥርዓት እንዲያውቅ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያውያን ያለንን አንድነት በተግባር የምናሳይበት ልዩ አጋጣሚ ነው ሲል ተናግሯል፡፡ 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህል ቡድን ተወካይ በአምላክ ታደሰ በመድረኩ የሚደረገው የባህል ልውውጥ ሕዝቦችን ይበልጥ የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የባህል ሳምንቱ ብሔራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ትስስርን ለማጎልበት ያለውን ሚና የሚያጎላ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የሐረሪ የባህል ቡድን ተወካይ ሙኒር ኢብራሂም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም